የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገራቱ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግም ይፋ አድርጓል፡፡
ሚኒስቴሩ ዛሬ በኢቦላ በሽታ ወቅታዊ ሁኔታዎችና በሽታው ወደ አገሪቱ እንዳይገባ እየተከናወኑ የሚገኙ የመከላከል ሥራዎችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ከአስር ወር በፊት በምዕራብ አፍሪካ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ በሽታ በአሁኑ ወቅት በላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ጊኒ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ስጋት እየሆነ መጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስትም በሽታው ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ጠንክሮ ከመስራት በተጨማሪ ባለበት ለማስቆም በሽታው በእጅጉ በተስፋፋባቸው አገሮች የተፈጠረውን የአቅምና ግብዓት ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት 210 በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን በሁለት ዙር ወደ አገራቱ ሊልክ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የጤና ባለሙያዎች ቡድኑ ሃኪሞችን፣ ነርሶችን፣ የፊልድ የኢፕዲሞሎጂ ባለሙያዎችን የሚያካትት ነው።
ቡድኑም በበሽታ ለተጠቁት ህሙማን የህክምና አገልግሎት፣ ከህመሙ ጋር ንክኪ ያላቸውን መለየትና መርዳት፣ የማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫና ንቅናቄ ስራ ይሰራል።
በአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር ካሎኮ ሲዲኪ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት ይህ ድጋፍ ለአለም በተለይ ደግሞ ለምዕራብ አፍሪካ አገራት ትልቅ አደጋ የሆነውን በሽታ ለማስቆም ትልቅ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር ሌሎችንም አገራት ለማነሳሳት ተምሳሌት ይሆናል።
ይህ ቡድን እስካሁን በጣም ፈታኝ ሆኖ የቆየውን ህብረተሰቡ ኢቦላ ላይ ያለውን አመለካከት ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሄ ያመጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጤና ባለሙያዎችና ፕሮግራሞች ብዛት ጥሩ የምትባል አገር መሆኗን የገለጹት ኮሚሽነሩ የአሁኑ ውሳኔ ግን ኢትዮጵያንም ሆነ አፍሪካ ህብረትን የሚያኮራ ነው ብለዋል።
የአለም የጤና ድርጅት ተወካይ የሆኑት ዶክተር ፒሬ ዕምፔሌ በበኩላቸው ይህን ውሳኔ አፍሪካዊ አንድነትና ትብብርን ከማጠናከሩም ባሻገር የአለም አቀፍ ማህብረሰብን ካንዣበበበት አደጋ የመታደግ ትልቅ መስዋትነት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን በማድረጓ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲናነቷን ብቻ ሳይሆን ወሳኝ አገር መሆኗንም አሳይታለች ብለዋል።
No comments:
Post a Comment