Tuesday, December 30, 2014

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በወህኒ ቤት ዘረፋ እንደተካሄደባቸው አስታወቁ


የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በወህኒ ቤት ዘረፋ እንደተካሄደባቸው አስታወቁ
‹‹በደምበኞቼ ላይ ዘረፋ ተፈፅሟል›› ጠበቃ ተማም አባቡልጉ
‹‹በህይወቴ ላይ የደህንነት ስጋት አለብኝ›› አቶ ሀብታሙ አያሌው
‹ከፍተኛ በደል ተፈፅሞብኛል›› አቶ ዳንኤል ሺበሺ

በእነ ዘላለም ወርቅነህ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ በወህኒ ቤት ውስጥ በመንግስት የደህንነት አባላት ዘረፋ እንደተካሄደባቸው ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡


በሽብርተኝነት ተወንጅለው ክስ የተመሰረተባቸው የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ የአረና ለትግራይ እና ሉዓላዊነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ልደታ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ቀርበዋል፡፡
በዕለቱ ችሎቱ ተሰይሞ የነበረው ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ፣ ተከሳሾች በቀረበባቸው የሽብር ክስ ላይ የሰጡትን መልስ በተመለከተ 7ኛ ተከሳሽ መልስ አሟልተው እንዲያቀርቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት፤ ምላሹን ለመስማት የነበር ቢሆንም ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ የተለየ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ፣ ደምበኞቻቸው ከሌሎች ተከሳሾች በተለየ መልኩ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን እና በደምበኞቻቸው ላይ ታህሳስ 12 ቀን ለታህሳስ 13 2007 ዓ.ም አጥቢያ ሌሊት ስምንት ሰዓት ላይ ዘረፋ መፈፀሙን እና በፍተሻውም የደምበኞቻቸው የግል ማስታወሻዎች፣ ገንዘብ እና በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ እያዘጋጁት የነበረው መቃወሚያና መከራከሪያ እንደተወሰደባቸው ገልፀዋል። አያይዘውም “ደንበኞቻቸው ላይ እየተደረገ ያለው ጉዳይ ለህይወታቸውም የሚያሰጋቸው መሆኑን እና ማረሚያ ቤቱ በሌሊት ፍተሻ ያደረጉባቸው ሰዎች፣ መርማሪዎቻቸው የነበሩ ሰዎችና ከማረሚያ ቤቱ ውጪ የሚገኙ ፖሊሶችና ደህነቶች መሆናቸውን” ገልፀዋል።
ድርጊቱ የተፈጸመው የተለየ የስም ዝርዝር ተይዞ ከሌሎች በተለየ መልኩ መሆኑን የገለጹት ጠበቃው፣ ‹‹ፍተሻው ስለት አልያም ሌላ ህገ-ወጥ ቁሳቁስ ለመያዝ የተደረገ አለመሆኑን ከተወሰዱት ንብረቶች ማየት ይቻላል›› በማለት ለፍርድ ቤቱ በደምበኞቻቸው ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አስረድተዋል፡፡
አቃቤ ህግ ብርሃኑ ወንድማገኝ፣ በበኩላቸው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ለእስረኞች ደህንነት ብሎ የተለያዩ ነገሮችን ሊያደርግ እንደሚችል ገልፀው አቤቱታው ከዛ አንፃር እንዲታይ ጠይቀል።
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ፣ በደምበኞቻቸው ላይ የተካሄደውን ፍተሻ ከህግ አንፃር ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ የተካሄደውን ፍተሻ በማስመልከትም ለፍርድ ቤቱ ‹‹በመሰረቱ ፍተሻ ሊካሄድ መቻሉ ላይ አይደለም አቤቱታው፡፡ የተካሄደው ፍተሻ ግን ህገ-ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍተሻው የተከናወነበት ሰዓት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ሳይሆን ሌሊት ከ8 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ፍተሻው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አይደለም የተከናወነው፡፡ በደህንነቶችና የፌደራል ፖሊሶች ነው ፍተሻው የተደረገው፡፡ ይህም ማረሚያ ቤቱ ደምበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ እንደሌለው ያሳያል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙት አካላትና በማን ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን›› በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። በተጨማሪነትም ፍርድ ቤቱ ከደምበኞቻቸው ላይ በፍተሻው ወቅት የተወሰዱባቸው ንብረቶችና ማስታወሻዎች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ምክትል ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከፍተኛ በደል እንደተፈፀመባቸው ገልፀው ፍርድቤቱ የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው፤ የመናገር ዕድል አግኝተው ‹‹እያልኩ ያለሁት በህይወቴ ላይ የደህንነት ስጋት አለብኝ ነው፡፡ ይህንን ስጋቴን ለችሎት እያስረዳሁ ነው፡፡ ግን እርስዎ ‹የበቀል እርምጃ› እንዲወሰድብን ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ በእርግጥ አሁንም የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድብን ማረጋገጫ የለንም፡፡ እሺ ለማን አቤት ይባላል? የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት ከማስረዳት ውጭ ለማን አቤት እንላለን?›› በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
የሀብታሙ አያሌውን አቤቱታ በማስመልከት መሃል ዳኛው ደረሰብኝ የሚሉትን ነገር እንደሚያጣሩ ገልፀው አሁን ላይ ቅሬታውን ማቅረቡ ማረሚያ ቤቱ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ ሊገፋፋው እንደሚችል ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ፣ በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ይህን ጉዳይ የማየት ስልጣን አለው ወይስ የለውም በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት እንዲሁም ተከሳሾቹ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የአቃቤ ህግን መልስ ለመስማት ለታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ ዋስትና ተከልክለው ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።


No comments: