
ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነ አንቶኖቭ 28 የመንገደኞች አውሮፕላን ከኡጋንዳ ኢንቴቤ ተነስቶ ወደ ሰንዓ የመን በመብረር ላይ እንዳለ ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ አቅራቢያ ለገዳዲ አካባቢ መከስከሱን ሪፖርተር ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ዘገበ። ጋዜጣው ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አገኘሁት ባለው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ሰኞ ማለዳ ከባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት የሬዲዮ ግንኙነት ከኢንቴቤ ተነስተው በኢትዮጵያ በኩል ወደ የመን ለመብረር ፈቃድ ጠይቀው ነበር፡፡ ባለሥልጣኑም የበረራ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል፡፡
ሪፖርተር በዘገባው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኤር ናቪጌሽን ክፍል ለአብራሪዎቹ የሚበሩበትን ከፍታ እንደሰጣቸውና አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን አየር ክልል አቋርጦ በማለፍ ላይ ሳለ አዲስ አበባ አካባቢ ሲደርስ የሞተር ብልሽት ሲያጋጥመው ይህንኑ ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ አሳውቆ ‹‹ኢመርጀንሲ ላንዲንግ›› እንደሚያደርግ (በድንገተኝነት እንደሚያርፍ) ሪፖርት አድርጐ፣ ከጠዋቱ 3፡35 ሰዓት ላይ ለማረፍ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በማምራት ላይ ሳለ ለገዳዲ አካባቢ መከስከሱን ዘግቧል።
“አደጋው እንደደረሰ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈልጐ ማዳን ቡድን ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሶ የአውሮፕላኑ አብራሪዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጉን” የዘገበው ሪፖርተር በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፋሪዎች እንዳልነበሩና፣ በአደጋው አብራሪዎቹ የተጐዱ ቢሆንም፣ ሕይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።
ሪፖርተር ዘገባውን ሲያጠናቅቅም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል ባለሙያዎች የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ አውሮፕላኑ ወደ ወደቀበት ሥፍራ በማምራት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ፤ ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ከተመረቱ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ በመሆኑ በየጊዜው እክል እየገጠማቸው በተለያዩ አገሮች በመከስከስ ይታወቃሉ፤ እነዚህ ዕድሜ ጠገብ አውሮፕላኖች ዋጋቸው ርካሽ በመሆኑ በአፍሪካ አገሮች በብዛት ይገኛሉ፤ ያረጁ በመሆኑና ተገቢ የሆነ ጥገና ስለማይደረግላቸው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ አደጋ እንደሚያደርሱ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያስረዳሉ ይላል።
No comments:
Post a Comment