የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ አስተማማኝ የሆነ የህዝብ የበላይነት፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነትና፣
ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ታላቅ ሃገራዊና ህዝባዊ ራዕይን አንግቦ በቁርጠኝነት የሚታገል፤ በታሪካችን ስር የሰደዱ ህዝባዊ
ችግሮቻችንን በመፍታት በምትኩ አስተማማኝና ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማምጣት፤ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወሳኝ ሃሳቦች ተመስርቶ፣
በወጣቶች የሚመራ ድርጅት ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ በአስተማማኝ ሁኔታ የበላይነቱን ተቀዳጅቶ በሃገሩ ላይ በነፃነት የመኖር
ተስፋው እንዲለመልም፤ እንዲሁም በህዝቧ ጠንካራ መተሳሰብና ፍቅር ላይ የተመሰረተች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ይቻል
ዘንድ፤ የዘረኛው ወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓትን ማስወገድ ብቻውን በቂ እንደማይሆን፤ ነገር ግን ከዚህ ጋር ተያይዞ የጥቂት ግለሰቦች ወይም
ቡድኖች የበላይነትና አምባገነንነት ከኢትዮጵያ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማክተም እንዳለበት ድርጅታችን በጽኑ ያምናል።
ይህ ታላቅ ሃገራዊ ራዕይ እውን እንዲሆንና ዘለቄታ ባለው መልኩ እንዲቀጥል ድርጅታችን ከወጠናቸው ዋና ዋና መሰረታዊ እቅዶች
መካከል ሁሉንም የዲሞክራሲ ሃይሎች ሊያሰባስብ፣ ሊያስተባብርና፣ ሊያቅፍ የሚችል ብሄራዊ የሽግግር ምክርቤት ማቋቋም በዋነኝነት
የሚጠቀስ እቅዳችን ነው። ይህንንም መሰረት በማድረግ ድርጅታችን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ተቋቁሞ ሁሉን አቀፍ
የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ መተዳደሪያ ህገ ደንብ እንዲኖርና ተግባራዊ እንዲሆን ግንባር ቀደም አስተዋዕፅዎ እያደረገ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የወጣቱ አስተዋዕፅዎ ወሳኝ መሆኑን
አጥብቆ ያምናል።በመሆኑም ማንኛውም የነፃነት ጉዞ ያለወጣቱ ተሳትፎ ከግቡ እንደማይደርስ በመረዳት ድርጅታችን በሽግግር
ምክርቤቱ ምስረታ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ የበኩሉን ሲያበረክት ቆይቷል። ይህንንም መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ
የሽግግር ምክርቤትን ለማቋቋምና፣ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ፣ ብሎም በአስተማማኝ ሁኔታ ላለመለት ራዕይ ከግቡ እንዲደርስ፤ በአለም
ዙሪያ የሚገኙ መላው አባላቱን ሁሉ በማሰማራት ባለው አቅምና ጉልበት የሚችለውን ሁሉ እያበረከተ ይገኛል። ለዚህም የሽግግር
ምክር ቤቱ በዳላስ ከተማ በኦፊሴል እስከተመሰረተበት እለት ድረስ ድርጅታችን አያሌ አባላቱን የሽግግር ምክርቤቱ በአለም ዙሪያ ባሉት
አስተባባሪ ኮሚቴዎች ውስጥ በአመራር ደረጃ ሲሰሩ መቆየታቸው እንደማሳያ ሊወሰድ ይችላል።
ስለሆነም ይህ በኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት የተጠራው ህዝባዊ የምክክር ጉባዔ አስፈላጊና ወቅታዊ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ
ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ የምክክሩ ተሳታፊ በመሆን የበኩላችንን እንደምናበረክት ቃል በመግባት ለተግባራዊነቱም በትጋት ከልብ
የምንሰራ መሆኑን በጥብቅ እናረጋግጣለን።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ጥሪ ወሳኝና ህዝባዊ ጥሪ እንደሆነ ታሪካዊ ምስክርናውን
በመስጠት፤ በዚህ ዘረኛ የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ከልክ ያለፈ ጭቆና ፣ ረገጣና ፣ እንግልት ደርሶብኛል የምትሉ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን
ዜጎችና ፣ በምንወዳት ሃገራችን ለህዝብ የሚበጅ ቀና ለውጥ ለዘለቄታው ይሰፍን ዘንድ የምትመኙ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ፤
እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ፣ የሲቪክ ማህበራት ታላቅ ሃገራዊ ሃላፊነትና የህዝብ አደራ
በጫንቃችሁ እንደተሸከማችሁ በመገንዘብ ፤ የሚጠበቅባችሁን ህዝባዊ ተልኮ መፈፀም ታሪካዊ ግዴታችሁ መሆኑን በመረዳት ፤
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ጎን እንድትቆሙ ሲል በጥብቅ እያሳሰበ ፤ ሃገራዊ ጥሪውን በአክብሮት ያቀርባል:: የኢትዮጵያ
ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ጥሪ የሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጥሪ ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ
No comments:
Post a Comment